ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ (1884 -1963ዓ/ም) ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ከአባታቸው ከመሪጌታ ወልደ ጻድቅ ሰሎሞን፤ ከእናታቸው ከወይዘሮ ወለተ ማርያም ባዩ (በኋላ እማሆይ ወለተ ማርያም) በሰሜን ሸዋ ዞን መርሐ ቤቴ አውራጃ ሚዳ ሚካኤል በተባለ ቦታ መጋቢት14 ቀን1884 ዓ.ም ተወለዱ:: በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት በዓርባ ቀናቸው በአጥቢያቸው ኮሶ ማርያም በተባለች ቤተ ክርስቲያን ተጠምቀው ገብረ ጊዮርጊስ ተብለው ስመ ክርስትና ተሠየሙ:: እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በዚያው በትውልድ ቀዬአቸው በአመልሳ ኮሶ ማርያም ግብረ ዲቁና ተምረው ከግብፃዊው የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳሳት አቡነ ማቴዎስ መዓርገ ዲቁና ተቀብለው ቤተ ክርስቲያን ሲያገለግሉ ቆዩ:: በመቀጠልም ወደታላቁ ገዳም ደብረ ሊባኖስ በመሄድ ጸዋትወ ዜማ፣ የቅኔና የመጻሕፍት ትርጓሜ ትምህርታቸውን ከመምህር ገብረ ኢየሱስ፣ የቅዳሴውን ትምህርት ከአባ ገብረ ሕይወት ተምረው አጠናቀቁ፡፡ ቅዱስነታቸው በዚህ ዓይነት ትምህርታቸውን በማስፋፋት፣ በዚያው በደብረ ሊባኖስ ገዳም ውስጥም በረድዕነት እያገለገሉ ሥርዓተ ገዳምን ሲማሩ ከቆዩ በኋላ ነሐሴ 24 ቀን 1905 ዓ.ም በ21 ዓመታቸው ሥርዓተ ምንኩስና ተፈጸመላቸው:: በ1906 ዓ.ም ከግብፃዊው የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳሳት አቡነ ማቴዎስ መዓርገ ቅስና ተቀበሉ። በ1909 ዓ.ም በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ትዕዛዝ በመናገሻ ግርጌ ለሚሠራው የቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ለሚጠጉ መነኮሳትና ባሕታውያን የሚሠሩትን መኖሪያ ቤቶች ግንባታ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኑን አስተዳደር ረዳት እንዲሆኑ በተጠየቁት መሠረት መነኮሳቱን እያስተማሩ ለሦስት ዓመታት በመናገሻ ቅድስት ማርያም ገዳም ቆዩ። በዚህ አንቅስቃሴ ላይ እያሉም ንግሥት ዘውዲቱ ያሠሯት የእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን በመጠናቀቋ በ1916 ዓ.ም የገዳሟ መምህር (አበ ምኔት) ሆነው ተሾሙ፡፡ በየካቲት 27 ቀን 1924 ዓ.ም የመናገሻ ቅድስት ማርያም ገዳምን መምህርነት እንደ ያዙ የአዲስ አበባ መንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ደብር አለቅነት በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተሾሙ፡፡ ሁለቱንም ቅዱሳት መካናት በትጋት እያስተዳደሩ ሳሉ በ1926 ዓ.ም በቅድስት ሀገር ኢየሩላሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ራይስ ሆነው ተሾሙ:: ከሁለት ዓመት አገልግሎት በኋላ ከኢየሩሳሌም ወደኢትዮጵያ በመምጣት በግርማዊነታቸው መልካም ፈቃድ የካቲት 24 ቀን 1927 ዓ/ም «ብፁዕ ዕጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ ዘነበረ በመንበረ ተክለ ሃይማኖት»ተብለው የታላቁ የደብረ ሊባኖስ ገዳም 59ኛ እጨጌ ሆነው ተሾሙ።
በዕጨጌነታቸው ዘመን የፋሺስት ወረራ ኢትዮጵያን ባጠቃ ጊዜ ቅዱስነታቸው ከሌሎች የቤተ ከርስቲያን አባቶች ጋር የቃል ኪዳኑን ታቦት በመያዝ በማይጨው ጦር ግንባር ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ተሰልፈው አብያተ ክርስቲያናትንና መጻሕፍትን የሚያቃጥል የምእመናንን ዘር የሚያጠፋ ጠላት መጥቷልና የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ በሃይማኖት፣ በጸሎት፣ በምህላ በርታ በማለት የኢትዮጵያን ሕዝብ ሲያጽናኑ ቆዩ። በኋላም ወደ ኢየሩሳሌም አቅንተው እስከ ድል ጊዜ ድረስ በስደት ቆይተዋል። ከፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ ድል በኋላም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት በጋራ ሆነው ከግብፅ ቤተ ክርስቲያን ጋር በጠላት ወረራ ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን ግንኙነት እንዲታደስና እንዲቀጥል ለማድረግ በየካቲት ወር 1934 ዓ/ም ንግግር ተጀመረ። ሆኖም የግብጽ ቤተ ክርስቲያን የጵጵስና ማዕርግ የመስጠትን ልምዳዊ መብቷን ለኢትዮጵያውያን አልለቅም በማለቷስፊና ረጅም ውይይት እንዲሁም ክርክር ተካሂዶ በሁለቱም አብያተ ክርስቲያናት ታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ካይሮ ሔደው ከተሾሙት ኢትዮጵያውያን አባቶች አንዱ በመሆን ሐምሌ 18 ቀን 1940 ዓ.ም «ብፁዕ አባ ባስልዮስ ጳጳስ ዘሸዋ ወለእጨጌ ዘደብረ ሊባኖስ» ተብለው ከአቡነ ቴዎፍሎስ፤ አቡነ ሚካኤል፤ አቡነ ያዕቆብ እና አቡነ ጢሞቴዎስ ጋር በእስክንድርያው ፓትርያርክ አቡነ ዮሳብ አንብሮተ እድ ተሾሙ፡፡
ከአራት ዓመት በኋላ ግብጻዊው አቡነ ቄርሎስም ካይሮ ላይ ስላረፉ ቀደም ሲል በተደረገው ስምምነት መሠረት ብፁዕ አቡነ ባስልዮስ ወደ ካይሮ ሔደው ጥር 6 ቀን 1943 ዓ.ም በአቡነ ዮሳብ እጅ ተቀብተው የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሊቀ-ጳጳሳ ሆኑ። በመቀጠልም በግብጽና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በተደረገ ስምምነት ከ11 ዓመታት የሊቀ ጵጵስና አገልግሎት በኋላ ሰኔ 21 ቀን 1951 ዓ.ም ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ በተገኙበት በካይሮ ቅዱስ ማርቀስ ቤተ ክርስቲያን በተደረገ ሥነ-ሥርዓት በፓፓው አቡነ ቄርሎስ 6ኛ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ተብለው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ሆነው ተሾሙ።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ በዘመነ ሥልጣናቸው ለቤተክርስቲያኗ ሰፋ ያለ አገልግሎት አበርክተዋል። 42 አብያተ-ክርስቲያነትን አሠርተዋል፡፡ 12 መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶችን አስፋፍተዋል፡፡ ለስብከተ ወንጌል አገልግሉት መፋጠንም በ1948 ዓ.ም የስብክተ ወንጌል ድርጅትን በማቋቋም ታላቅ ሥራን ሠርተዋል:: ቤተ ክርስቲያኗ ከዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ጋር የሠመረ ግንኙነት አንዲኖራት፣ ምእመናን በሥርዓተ ቤተክርስቲያን እንዲተዳደሩ፣ አስራ ሰባት የሚደርሱ ኤጲስ ቆጳሳትን በመሾም፣ የቤተ ክርስቲያኗንም አሀጉረ ሰብከት ዓሥራ ስድስት አድርሰዋል፡፡ ብዙዎቹ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕንፃዎችና የመኖሪያ ቪላዎች የተሠሩት በእሳቸው የአገልግሉት ዘመን ነው፡፡ በነበራቸው ላቅ ያለ አገልግሎት የተነሣ የግርማዊ ቀዳማዊ ዓፄ ኃይለ ሥላሴን የመጀመረያ የክብር ኮከብ ኒሻን ተሸልመዋል፡፡
ቅዱስናቸው በእድሜ ዘመናቸው የጤናቸው ሁኔታ እያሽቆለቆለ በመጣ ጊዜ በደብረ ሊባኖስ ገዳም በጸሎትና በመንፈሳዊ ተግባራት ላይ በማተኮር ብዙ ጊዜያቸውን አሳልፈዋል። በመጨረሻም ፓትርያርኩ በተወለዱ በ79 ዓመት ዕድሜያቸው ጥቅምት 02 ቀን 1963 ዓ/ም አርፈው ጥቅምት 04 ቀን 1963 ዓ/ም ንጉሠ ነገሥቱ ዓፄ ኃይለ ሥላሴ፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች በተገኙበት በደብረ ሊባኖስ ተቀበሩ። አቡነ ባስልዮስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን ባደረጉት አስተዋጽኦ የተከበሩና ለእምነት ባላቸው ቁርጠኝነት የሚታወሱ ናቸው።
በአሁኑ ጊዜም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የደብረ ብርሃን ቅዱስ ባስልዮስ መንፈሳዊ ኮሌጅ መሥራችና የበላይ ኃላፊ ሐሳብ አመንጭነት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ስም መንፈሳዊ ኮሌጅ ተከፍቶ በሥነ መለኮት፣ በሕግ፣ በቱሪዝምና ቅርስ አስተዳደር ለመማር መሥፈርቱን የሚያሟሉ ደቀመዛሙርትን ከየአህገረ ስብከቱ ተቀብሎ በመደበኛና በተከታታይ ትምህርት እያስተማረ ይገኛል፡፡ በመሆኑ ኮሌጁ የተማረ የሰው ኃይል በማፍራት ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ተጨማሪ ሊቃውንትን በማፍራት ረገድ የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማድረግ በከፍተኛ ጥረት ላይ ይገኛል።
ምንጭ፡- መርስኤ ኀዘን ወወልደ ቂርቆስ፡፡(1956)፡፡ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያው ፓትረያርክ 1951 ዓ.ም፡፡ አዲስ አበባ፣ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፡፡